ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው።
እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፦ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው።
ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቆሙ።
ሳውልም ከምድር ተነሣ፥ አይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት።
ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም።
በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ፦ ሐናንያ ሆይ፥ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ አለ።
ጌታም፦ ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤
እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል አለው።
ሐናንያም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤
በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ።
ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤
ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።
ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት፦ ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ።
ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥
መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ።
ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ።
![](https://i.ytimg.com/vi/PcJB4vHWhQ4/maxresdefault.jpg)